Home "ከጥገኝነት ወደ ነፃነት፤ የልህቀት ማዕከሉ እና የኢንዱስትሪው አዲስ የፓርትነርሺፕ ትስስር"

"ከጥገኝነት ወደ ነፃነት፤ የልህቀት ማዕከሉ እና የኢንዱስትሪው አዲስ የፓርትነርሺፕ ትስስር"

28th April, 2026

(ክፍል አምስት )

🇪🇹አዲስ አበባ | መጋቢት 14/2018 ዓ.ም🇪🇹 

የፌዴራል ሥራና ክህሎት ሚኒስቴር የነደፈውን አዲሱን የ2017 የቴክኒክና ሙያ ስትራቴጂ ተከትሎ፣ የሰልጣኞች የሥልጠና ባለቤት እንዲሆን የተቀመጠው የኢንዱስትሪው ሚና በተጨባጭ መሬት እያረፈ ይገኛል። 

የምርታማነትና ማሻሻያ የልህቀት ማዕከል ዋና ዲን አቶ አድማሱ በቀለ፣ ከኮሚኒኬሽን ዳይሬክቶሬት ከፍተኛ የሕዝብ ግንኙነት ባለሙያ ጋር ባደረጉት የመጨረሻ ክፍል ቆይታ፤ ማዕከሉ ከኢንዱስትሪዎች ጋር የፈጠረውን ጠንካራ ትስስር እና ያጋጠሙ ተግዳሮቶችን በሚከተለው መልኩ አብራርተዋል። 

የኢንዱስትሪዎች እምነት እና የሀብት ውህደት

"በመንግስት ተቋም ውስጥ ማሽን አይነካም፣ ምርት አይመረትም የሚለው አሮጌ አስተሳሰብ አሁን ተሰብሯል" የሚሉት አቶ አድማሱ፤ ኢንዱስትሪዎች በማዕከሉ ላይ ያላቸው እምነት በከፍተኛ ሁኔታ መጨመሩን ገልጸዋል። ለዚህም ማሳያ የሚሆነው፦

የጋርመንት ማሽኖች ዝርጋታ፦ አንድ ትልቅ ኩባንያ በሚሊዮን የሚቆጠር ዋጋ ያላቸው የጋርመንት ማሽኖችን በማዕከሉ ወርክሾፕ ውስጥ ተክሎ ለማምረት ስምምነት ፈጽሟል። ይህም ማዕከሉ እያሰለጠነበት፣ ኩባንያው እያመረተበት ሁለቱም የሚጠቀሙበት አዲስ የትብብር ሞዴል ነው። 

የሀገር ውስጥ ፋብሪኬሽን (Fabrication Shop)፦ ከዚህ ቀደም የከፍተኛ ቮልቴጅ ኬብል (High tension cable) እቃዎችን ከቻይና የሚያስመጣ አንድ ትልቅ ኩባንያ፣ አሁን በማዕከሉ ወርክሾፕ ውስጥ ከባለሙያዎች ጋር በጋራ ማምረት ጀምሯል።

የፈጠራ ባለሙያዎች ማቆያ (Incubation) እና የ"30/70" ሞዴል ማዕከሉ የፈጠራ ሐሳብ ያላቸውን ወጣቶች ወደ ኢንዱስትሪ የማሸጋገር (Incubate የማድረግ) ሥራውን አጠናክሮ ቀጥሏል። ከውጭ የሚገቡ ዊልቼሮችንና ክራንቾችን በሀገር ውስጥ ምርት (ቀርከሃ) መተካት የጀመረ አንድ የፈጠራ ባለሙያ በማዕከሉ ድጋፍ እየተደረገለት ይገኛል። 

ማዕከሉ ቦታ፣ የማሽንና የባለሙያ ድጋፍ በማድረግ ባለሙያው ምርቱን ማምረትና መሸጥ እንዲጀምር አድርጓል። አሁን ይህ ሞዴል አድጎ ወደ ፓርትነርሺፕ በመቀየር፣ ማዕከሉ ከሚገኘው ትርፍ 30% ተቋዳሽ መሆን የጀመረበት አዋጭ አሰራር ተፈጥሯል።

የስትራቴጂው ድል፦ የጠባቂነት መንፈስን መስበር

አቶ አድማሱ እንደገለጹት፤ አዲሱ ስትራቴጂ እና 11ዱ የዘረመል (DNA) እሳቤዎች ተቋማትን ከእንቅልፋቸው አንቅተዋል። ቀደም ሲል ተቋማት ማሽኖችንና ሰፊ ወርክሾፖችን ይዘው ከመንግስት በጀት ብቻ የሚጠብቁበት አሰራር ነበር። 

አሁን ግን በዲጂታላይዘሽንና በኢንተርፕሪነርሽፕ በመታገዝ ራስን የመቻል መንፈስ ተፈጥሯል። አቶ አድማሱ "እንደ ኢትዮጵያ አየር መንገድ የራስህን ገቢ እያመነጨህ ራስህንም ችለህ አገርንም መደጎም እንደሚቻል ማሳያ ነው" ብለዋል። ስትራቴጂው ተቋማት ገቢ እንዲያመነጩ ነፃነት የሰጠ በመሆኑ፣ ማዕከሉ ዛሬ የያዛቸውን 7 የንግድ ፈቃዶች ወደፊት ወደ 15 ለማሳደግ የማንንም ፈቃድ መጠበቅ እንደማይጠበቅበት በልበ ሙሉነት ገልጸዋል።

ያሉ ተግዳሮቶች እና የወደፊት ተስፋ

ምንም እንኳን ትልልቅ ስኬቶች ቢመዘገቡም፣ ገና ያልተቀረፉ ተግዳሮቶች መኖራቸውን ዋና ዲኑ አልሸሸጉም። ከእነዚህም መካከል፦

አዲስ ለውጥን የመቀበል ችግር፦ ከነባሩ የሥራ ባህል ወጥቶ አዲስ ቴክኖሎጂና አሰራርን ለመቀበል የሰው ኃይልን የማሳመን ሂደት ጊዜ የሚወስድ መሆኑ፤

የመመሪያዎች መዘግየት፦ ፖሊሲውና ስትራቴጂው ቢወጡም፣ ዝርዝር የአሰራር መመሪያዎች ገና ባለመምጣታቸው የሚፈጠሩ የአተገባበር ክፍተቶች፤

የሀብትና የፍላጎት አለመመጣጠን፦ ከአዲሱ እሳቤ ጋር ለመራመድ የሚያስፈልገውን ትልቅ የፋይናንስ አቅም በአንድ ጊዜ ለማሟላት የሚደረገው ጥረት ተጠቃሽ ናቸው። 

ዋና ዲኑ አቶ አድማሱ በቀለ ማብራሪያቸውን ሲያጠቃልሉ፤ ተግዳሮቶች ቢኖሩም ማዕከሉ ባለፈው አንድ ዓመት ውስጥ በሰው ኃይልና በመሠረተ ልማት ያመጣቸው ለውጦች ተስፋ ሰጪ መሆናቸውን ጠቁመው፣ ኮሌጆችም ያላቸውን እምነት አሳድገው ይህንን የተገነባ አቅም እንዲጠቀሙ ጥሪያቸውን አስተላልፈዋል።

.

Copyright © All rights reserved.

Created with