"ወደ ዲጂታል ዘመን፤ የምርታማነትና ማሻሻያ የልህቀት ማዕከል የትራንስፎርሜሽን ጉዞ"
(ክፍል ሦስት)
🇪🇹አዲስ አበባ | መጋቢት 11/2018 ዓ.ም🇪🇹
የፌዴራል ሥራና ክህሎት ሚኒስቴር የቀረጸውን አዲሱን የ2017 የቴክኒክና ሙያ ስትራቴጂ ተከትሎ፣ ነባር ተቋማትን በአዲስ መንፈስ የማደራጀት ስራ በስፋት እየተከናወነ ይገኛል። ከእነዚህም መካከል በ1962 ዓ.ም የተመሰረተውና ረጅም እድሜ ያስቆጠረው የምርታማነትና ማሻሻያ የልህቀት ማዕከል፣ ራሱን ከዘመኑ ጋር በማዛመድ ወደ "ዲጂታል የልህቀት ማዕከልነት" ለመሸጋገር ስር ነቀል ለውጦችን እያደረገ ይገኛል።
የማዕከሉ ዋና ዲን አቶ አድማሱ በቀለ፣ ተቋሙ በገለልተኛ ወገን (Technobizia) በተጠና ጥናት መሠረት የጀመረውን የለውጥ ጉዞ በሚከተለው መልኩ አብራርተዋል።
ከስያሜ እስከ አደረጃጀት፦ አዲሱ "Entrepreneurship & Technical Skill" ማዕከል
ተቋሙ ሲመሰረት የነበረው ተልዕኮና የነበሩት ማሽነሪዎች አሁን ካለው የቴክኖሎጂ እድገት ጋር የማይሄዱ በመሆናቸው፣ አዲስ የለውጥ ደንብ ተዘጋጅቷል። በዚህም መሠረት ተቋሙ ስሙን ወደ "Entrepreneurship & Technical Skill Center of Excellence" በመቀየር፣ በዋናነት በሥራ ፈጠራ (Entrepreneurship) እና በላቀ የቴክኒክ ክህሎት ላይ ያተኮረ አደረጃጀት ይዞ ይወጣል። ዓላማውም ተቋሙ ራሱ የፈጠራ ማዕከል ሆኖ እንዲታይና ሌሎች ኮሌጆችን በሰው ኃይልና በማሽነሪ ብቃት መደገፍ እንዲችል ማድረግ ነው።
ማዕከሉን ወደ ሙሉ ዲጂታል አገልግሎት ለማሸጋገር ትልቅ ስራ መጀመሩን የገለጹት አቶ አድማሱ፣ የሚከተሉትን አበይት ተግባራት ጠቅሰዋል፦
የስማርት ክፍሎች (Smart Classes) ግንባታ፦ በዲጂታል የታገዘ ስልጠና የሚሰጥባቸው 20 ዘመናዊ ስማርት ክፍሎችን ለማደራጀት አንድ ባለ G+4 ህንፃ ተለይቶ ተዘጋጅቷል። ከኢትዮ ቴሌኮም ጋር የተደረገ ስምምነት፦ ለዲጂታል ኢንፍራስትራክቸር ግንባታው ከኢትዮ ቴሌኮም ጋር ለማካሄድ የቅድመ ዝግጅት ስራዎችና የከተማ አስተዳደሩ ውሳኔ በመጠበቅ ላይ እንገኛለን።
የማሽነሪዎች ሽግግር፦ ከ1962 ጀምሮ የነበሩ አሮጌ (Conventional) ማሽኖች እየተነሱ፣ በዘመናዊ የCNC ዲጂታል ማሽኖች የመተካት ስራ በስፋት እየተሰራ ነው።የኢንኩቤሽን አገልግሎትና የ3 ዓመቱ የልህቀት ጉዞ ማዕከሉ የፈጠራ እሳቤ ያላቸው ባለሙያዎች ሃሳባቸውን ወደ ተግባር የሚቀይሩበት የ"ኢንኩቤሽን" አገልግሎት መስጠት ጀምሯል። ለዚህም የፈጠራ ስራቸው ጊዜ የሚወስድባቸው ባለሙያዎች አርፈው መስራት እንዲችሉ የዶርሚተሪና ሌሎች መሠረተ ልማቶች ግንባታ በ3 ዓመት ውስጥ ተጠናቆ እንዲያልቅ ግብ ተቀምጧል።
አቶ አድማሱ እንደገለጹት፣ ይህ ሁሉ ጥረት አዲሱ ስትራቴጂ ያስቀመጣቸውን አራት ምሶሶዎችና "ስልጠና ከዳቦ በላይ" የሚለውን እሳቤ ተግባራዊ ለማድረግ ያለመ ነው። ተቋሙ አሁን ላይ ከ70% በላይ የሚሆነውን የዝግጅት ጉዞ በማጠናቀቅ ላይ እንደሚገኝም አረጋግጠዋል።
በቀጣይ ክፍል (የመጨረሻ ክፍል) የሚመለሱ ነጥቦች፦
በተቋሙ ላይ የሚነሱ ቅሬታዎችና ምላሾቻቸው፤ የPLC እንቅስቃሴና ተቋሙ በገቢ ራሱን ለመቻል እያደረገ ያለው ጥረት፤ የግል ባለሀብቶች ተሳትፎና በአዲሱ የ2017 ስትራቴጂ ዙሪያ ያሉ ተግዳሮቶችና ተስፋዎች።
ከዋና ዲኑ ጋር የተደረገው የመጨረሻ ክፍል በቅርብ ሰዓት ይጠብቁን።



.