(ክፍል ሁለት)
🇪🇹አዲስ አበባ | መጋቢት 10/2018 ዓ.ም🇪🇹
የፌዴራል ሥራና ክህሎት ሚኒስቴር የቴክኒክና ሙያ ዘርፉን ወደ አዲስ ምዕራፍ ለማሸጋገር የቀረጸው አዲሱ ስትራቴጂ፣ ተቋማት ከቆየውና ከተለመደው "ለሥልጠና ብቻ" ከሚል የተገደበ እሳቤ ወጥተው፣ ተጨባጭ የኢንዱስትሪ ችግር ፈቺ እና የቴክኖሎጂ ሽግግር ማዕከል እንዲሆኑ ያዝዛል።
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ሥራና ክህሎት ቢሮም በስሩ ያሉ 6 ፖሊ ቴክኒክና 8 ኮሌጆችን እንዲሁም የምርታማነትና ማሻሻያ የልህቀት ማዕከልን ጨምሮ በአጠቃላይ 15 ተቋማትን በማስተባበር ይህንኑ "ከስልጠና በላይ" የሚለውንና 11ዱን የክህሎት-መር (DNA) እሳቤዎች ወደ መሬት የማውረድ ስራ እየሰራ ይገኛል።
በዚህ ሂደት ውስጥ የምርታማነትና ማሻሻያ የልህቀት ማዕከል ስትራቴጂውን ተከትሎ የሰውን ኃይል የማብቃትና የቴክኖሎጂ ሽግግርን የማፋጠን ስራውን በልዩ ትኩረት እያከናወነ ይገኛል።የማዕከሉ ዋና ዲን አቶ አድማሱ በቀለ፣ ማዕከሉ በስትራቴጂው መሠረት የሚሰጣቸውን ልዩ አገልግሎቶችና ከኢንዱስትሪው ጋር ያለውን ተግባራዊ ትስስር በተመለከተ የሚከተለውን ማብራሪያ ሰጥተዋል።
ትኩረቱን በሦስት ዋና ዋና አካላት ላይ ያደረገ "ክፍተት-መር" ስልጠና ማዕከሉ እንደ ሌሎች ኮሌጆች መደበኛ ስልጠና የማይሰጥ ሲሆን፣ ስልጠናዎቹ በዋናነት በሦስት ወሳኝ የሰው ኃይል አካላት ላይ ብቻ ያተኮሩ ናቸው። እነሱም፦
የቴክኒክና ሙያ አመራሮች፦ በየደረጃው ለሚገኙ የኮሌጅ አመራሮች (ለዲኖች፣ ለምክትል ዲኖችና ለዲፓርትመንት ኃላፊዎች) የሚሰጥ የአመራር ብቃት ስልጠና፤
አሰልጣኞች፦ በመንግሥት ተቋማት ለሚያሰለጥኑ የቴክኒክና ሙያ መምህራን የሚሰጥ የክህሎት ማሻሻያ ስልጠና፤
የኢንዱስትሪ ባለሙያዎች፦ በልምድም ሆነ በተለያዩ የትምህርት ዘርፎች ወደ ኢንዱስትሪው ገብተው የሚሰሩና ከወቅቱ ቴክኖሎጂ ጋር ለመቀናጀት የክህሎት ማሻሻያ (Upgrade) ለሚያስፈልጋቸው ባለሙያዎች የሚሰጥ ስልጠና ናቸው።
አቶ አድማሱ እንደገለጹት፣ እነዚህ ስልጠናዎች በዘፈቀደ የሚሰጡ ሳይሆኑ፣ ተጨባጭ የአፈጻጸም ክፍተቶች ቀድመው ተዳስሰውና ተለይተው (Gap Assessment Based) ክፍተቱን ለመሙላት ብቻ የሚከናወኑ ናቸው።
የኢንዱስትሪዎች ተሳትፎና የቴክኖሎጂ ሽግግር
አዲሱ ስትራቴጂ ኢንዱስትሪው የስልጠናው ማዕከልና ባለቤት እንዲሆን ያስቀምጣል። እስከ አሁን የነበረው ትልቁ ተግዳሮት ኢንዱስትሪዎች ሰልጣኞችን ከመውሰድ ባለፈ ተቋሙን እንደ ባለቤት አለማየታቸው እንደነበር የገለጹት ዋና ዲኑ፣ አሁን ግን በተግባር የታገዘ የቴክኖሎጂ ፍላጎታቸው እየጨመረ መጥቷል ብለዋል።
ባለፉት 6 ወራት ብቻ ከ300 በላይ ከሆኑ የተለያዩ ኢንዱስትሪዎች ለተውጣጡ ባለሙያዎች በተለያዩ ዘርፎች ስልጠና ተሰጥቷል። ለምሳሌ፦
በእንጨት ስራ ዘርፍ፦ አብዛኛው ፋብሪካ የሚገለገለው በCNC ማሽን በመሆኑ፣ በኮምፒውተር ያለቀለትና በቴክኖሎጂ የታገዘ የዲዛይን (Software) ስልጠና በማዕከሉ እየተሰጠ ይገኛል።
በአውቶሞቲቭ (Automotive) ዘርፍ፦ ኢንዱስትሪዎች ከማዕከሉ ጋር በቅርበት እየሰሩ ካሉባቸው ዘርፎች ቀዳሚው ሲሆን፤ ማሽንንግ (Machining & Welding)፣ ኤሌክትሪክ እና አይሲቲ (ICT) ዘርፎችም ኢንዱስትሪዎች አገልግሎቱን በስፋት እየተጠቀሙባቸው ይገኛል።
በቀጣይ ክፍል (ሦስት) ተቋሙ "የልህቀት ማዕከል" (Center of Excellence) የሚለውን ስያሜውን የሚመጥን ምን አይነት ተግበራትንና ሞዴል እንደሚከተል፤ በአዲሱ ስትራቴጂ መሠረት ከመንግስት ድጎማ ሙሉ በሙሉ ወጥቶ በራሱ ገቢ የመተዳደር አቅም አለው ወይ ለሚሉት ጥያቄዎች የዋና ዲኑ ምልሽ ይጠብቁን፡፡




.